Sunday, January 29, 2012

አትጨነቅ


ንብረት አጣሁ ብለህ 
            በሃሳብ አትለቅ ፣
ንብረት ጤንነት ነው
            ፀጋህን አትናቅ፣ 
መልክ የለኝም ብለህ 
           እንዳትዘናጋ ፣
በአምሳሉ ፈጥሮሃል
           አልፋና ኦሜጋ፣
ስልጣን ስለሌለህ 
           ልብህ እንዳያዝን፣ 
ስልጣን ተሰጥቶሃል
            የአምላክ ልጅ ለምሆን፣ 
ወገን የለኝ ብለህ
             ምን ያስጨንቅሃል
ከቅዱሳን ጋራ
             ባለ ሀገር ሆነሃል። 

ፍቅር


ፍቅር.......... እግዚአብሔር ነው።(ዮሐ፬፥፰-፩፮ )
ፍቅር.......... ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ነው።(ዮሐ፬፥፯)
ፍቅር..........በመንፈስ ቅዱስ ለኛ ተሰጠ።(ሮሜ፭፥፭)
ፍቅር..........እግዚአብሔርን መውደድ ነው።(ማቴ፳፪፥፴፯-፴፱)  
ፍቅር..........ባለንጀራን መውደድ ነው።(ማቴ፳፪፥፵)  
ፍቅር..........የምግባራት ሁሉ ራስ ነው። 
ፍቅር..........ታጋሽ ናት፤ በጎም ናት።  
ፍቅር..........አትቀናም አትመካም   
ፍቅር..........አትነፍግም፤ ፊቷንም አታጠቁርም    
ፍቅር..........ገንዘብን አትሻም፤ አትቆጣም።   
ፍቅር..........በእውነት እንጅ በኃጢአት ደስ አይላትም።     
ፍቅር..........ሁሉን ትችላለች፤ሁሉን ታምናለች።
ፍቅር..........ሁሉን ተስፋ ታደርጋለች።
ፍቅር..........ሁሉን ትታገሳለች፤ ትፈፅማለች(፩ቆሮ፲፫፥፬-፯)
ፍቅር..........ስራን ሁሉ ትሰራለች(ገላ፭፥፲፭)
ፍቅር..........ለዘወትር አትወድቅም(፩ቆሮ፲፫፥፰)
ፍቅር..........የሕግ ሁሉ ፍፃሜ ናት።
ምንጭ፦ሐመር ፲፱፺ ዓ/ም(፮ኛ ዓመት ቁጥር ፬ ) 

Wednesday, January 4, 2012

«ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን፥ ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤»

«ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን፥ ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤»
ማቴ ፭፥፴፰።


ከሊቀ ኅሩያን ከፈለኝ ወልደ ጊዮርጊስ
ይህ ቃል፦ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በምንም ነገር ቢሆን መማል ፈጽሞ እንደማይገባ ከተናገረ በኋላ የተናገረው ቃል ነው። እኔም እውነት የሆነውን እውነት፥ ሐሰት የሆነውን ደግሞ ሐሰት ለማለት ይኽንን ሕያው የሆነውን የጌታዬን የአምላኬን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል መነሻ አድርጌያለሁ።
ቅዱሳን አባቶቻችን ጥንተ ጠላታቸው ሰይጣን የተለያየ ክብረ ነክ ስድብ ሲሰድባቸው በትእግሥት ያሳለፉት፥ በአኰቴት ይቀበ ሉት ነበር። ስለ ሃይማኖታችው መዋረድ ለእነርሱ ጸጋ ነውና። ቅዱስ ዳዊት ከዙፋኑ ወርዶ ከተርታው ሕዝብ ጋር ተሰልፎ በመዘመሩ ሜልኰል ወለተ ሳኦል አሽሟጣው ነበር፥ እርሱ ግን ሽሙጡን በጸጋ ተቀብሎ ስለ እግዚአብሔር ክብር ገና ከዚህ የበለጠ ራሱን እንደ ሚያዋርድ ነግሯታል። ፪ኛ ሳሙ ፮፥፳-፳፪። የገዛ ልጁ አቤሴሎም አሳድዶት በስደት በሚንከራተትበትም ጊዜ የሳኦል ቤተ ዘመድ የሆነ፥ ሳሚ የሚባል ሰው በሕዝቡና በመኳንንቱ ፊት ሰድቦታል። ይህ በዳዊት ላይ የወረደ ስድብና ውርደት ያሳዘናቸውና ያበሳጫቸው የሶር ህያ ልጆች ሰይፋቸውን መዝዘው ነበር። በዚህን ጊዜ ቅዱስ ዳዊት፦ «ተዉት ይስደበኝ፤ (ይርገመኝ፥ ያዋርደኝ፤)፤» ብሎአቸዋል። በየዘ መኑ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንም ስድቡን ብቻ ሳይሆን ሰይፉን፥ እሳቱን፥ ግርፋቱን ሁሉ ታግሠው እስከ ሞት ድረስ ጸንተዋል። «እስከ ሞት ድረስም የታመንህ ሁን፤ የሕይወት አክሊልንም እሰጥሃለሁ።» የተባለውን በተግባር ፈጽመዋል። ራእ ፪፥፲። በሃይማ ኖታቸው ሲመጡባቸው ግን ትእግሥት የላቸውም፥ «መናፍቅ» ሲሉአቸው ዝም አይሉም።
እኔ ይኽንን መግለጫ ከአምስት ዓመታት በኋላ እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ለማውጣት የተገደድኩት፥ በ2002 ዓ.ም. በተከበሩ በመምህር ሀብተ ማርያም ተድላ በተጻፈ መጽሐፍ ላይ እና በሰሞኑ ለቅድስት ተዋህዶ ሃይማኖት ለመሠዋት በተዘጋጁ የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ወጣቶች ለቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ተሃድሶ መናፍቃን ባቀረቡት አቤቱታ ላይ «ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ፤» ሆኜ በመገኘቴ ነው።
አባታችን መምህር ሀብተ ማርያም ተድላ፥ በዲሲ እና አካባቢዋ አብያተ ክርስቲያናት ትብብር ተቋቁሞ በነበረው የካህናት ማኅበር፥ በ«ቄስ» አስተርአየ ጽጌ፤ አቅራቢነት ተነሥቶ የነበረውን የሃይማኖት ክርክር 219 ገጽ በሆነው መጽሐፋቸው የማያዳግም ኦርቶ ዶክሳዊ መልስ ሰጥተዋል። ይህም በዘመናቸው ለተነሡ መናፍቃን በአፍም በመጽሐፍም መልስ ከሰጡ ጥንታውያን ሊቃውንት ጋር የሚያሰልፋቸው ነው። በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ዙሪያ፦ «ጥንተ አብሶ ነበረባት፤» በሚሉ ወገኖችና «ጥንተ አብሶ አልነ በረባትም፤» በሚሉ ወገኖች መካከል ዱላ ቀረሽ ክርክር በሚደረግበት ጊዜ እኔም በቦታው ተገኝቼ ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ የማገለ ግለው ዲሲ ማርያም ስለነበረ ነው። የጉባኤውም ቃለ ጉባኤ ጸሐፊ ነበርኩኝ። የጉባኤው ሰብሳቢም ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ነበሩ።
ይህ የሃይማኖት ክርክር በሚደረግበት ወቅት፦ የ«ቄስ» አስተርአየን ሃሳብ የደገፉ ሰዎች ዝርዝራቸው በመጽሐፉ ላይ ተጠቅሷል። ይኽንን ፍጹም የሆነ ክህደት ከተቃወሙት መካከል ደግሞ እኔ እና ርዕሰ ደብር አብርሃም እንገኝበታለን። ይኽንንም በወቅቱ በስደት እዚህ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፥ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ የነበሩት አቡነ ማትያስ፥ ያውቁታል። በኋላም ለሀገረ ስብከቱ ተሹመው መጥተው ለነበሩት ለብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ሁሉንም ነገር አስረድቼ ማስረጃዎችን ሰጥቻቸዋለሁ። ጸሐፊው መምህር ሀብተማርያም ተድላ በመጽሐፋቸው ገጽ 34 ላይ፦ «ለቅዱስ ሲኖዶስ በተላከው በማኅበረ ካህናቱ ጽሑፍ አለመግባባት የተፈጠረበት ምክንያት ከሚለው አርእስት ቀጥሎ የሰፈረው ይነበባል። አንደኛው ወገን፦ < አንጺሖ ሥጋሃ ኃደረ ላዕሌሃ> የሚለውን ቃል ተቀብሎ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የነቢብ፥ የገቢር፥ የኀልዮ ኃጢአት ያልነበረባት የሌለባት ናት። ነገር ግን በአዳማዊ ዘር በኲል ከሚተላለፈው ውርስ መንፈስ ቅዱስ አንጽቷታል ሲል፤ ሁለተኛው ወገን ደግሞ ገና ሳትወለድ በዘር ይተላለፍ ከነበረው አዳማዊ ውርስ ነጻ ናት የሚል ነው፤» ብለዋል። ይህ ትክክል ነው። ትክክል ያልሆነው ይኽንን የተረጐሙበት መንገድ ነው። «ይህ ከዚህ በላይ የሚነበበው የማኅበረ ካህናት ጽሑፍ የተጣመመና የተዛባ (Distorted) በሆነ አጻጻፍ የተቀመጠ ወይም ለማደናገር ሆን ተብሎ የተደረገ አሻሚ ሁኔታ ይታይበታልና መስተካከል ይኖርበታል፤» ብለዋል። ይህም በወቅቱ «እመቤታችን ጥንተ አብሶ አልነበረባትም፤» ብለን የተከራከርነውን ሰዎች እምነት የነካ ነው። ምክንያቱም «ጥንተ አብሶ አልነበረባትም፤» የሚለው የገባው የእኛን እምነት ለማንጸባረቅ እንጂ ለማደናገር አይደለምና ነው። አባታችን መምህር ሀብተ ማርያም ይኽንን ያደረጉት ሆን ብለው እንዳልሆነ ስለሚገባኝ ለወደፊቱ እንዲስተካከልልኝ በትኅትና እጠይቃለሁ።
ምንአልባት በወቅቱ ምን እርምጃ ወሰድክ የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል፥ ተገቢም ነው። ኅዳር 1 ቀን 1998 ዓ.ም. ስድስት ገጽ የቅሬታና የአቋም መግለጫ በማውጣት በጽሑፍ አሰራጭቻለሁ፥ በሬድዮም አስነግሬአለሁ። በዚህም ምክንያት ከዲሲ ማርያም ከሥራዬ ተባርሬ እስከነ ቤተሰቤ በረሀብ አለንጋ ተገርፌአለሁ። በኋላም ቅዳሜ ቅዳሜ አገለግል ወደነበረበት በሪችመንድ ደብረ መንክራት ልደታ ለማርያም ቤተክርስቲያን ብቻ ተወስኜ በምኖርበት ጊዜ፥ ቤተክርስቲያኗን ወደ እናት ቤተክርስቲያን በማስገባቴ ብዙ ፈተና ደርሶብኛል። ከፈተናውም አንዱ፥ የዲሲ ማርያም አስተዳደር ሪችመንድ ከሚገኘው ቦርድ ጋር በመመሳጠር ፍርድ ቤት ገትረውኛል። ይኽንንም ብፅዕ አቡነ ገብርኤል ያውቁታል። ምክንያቱም ቦርዱ በምስክርነት ጠርቷቸው ፍርድ ቤት ተገኝተው ስለነበረ ነው። መገኘታቸውም በእኔ ላይ ለመመሥከር ሳይሆን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለማክበር ሲሉ ብቻ ነበር። ነገር ግን ከሳሾቼ ምንም ማስረጃ ማቅረብ ስላልቻሉ ክሳቸውን ለማቆም ተገደዋል። ዳኛውም ለእኔ ፈርዶልኝ ፋይሉን ዘግቶታል። የእኔ አቋም በግልፅ የታወቀ በመሆኑ ከአሁን ቀደም ከብፁዕ አቡነ ማትያስና ከብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ጋር አሁንም ከብፁዕ አቡነ አብርሃም ጋር እናት ቤተክርስቲያኔን እያገለገልኩ ነው። ሃይማኖቴም የጠራ ነው። በመሆኑም «መናፍቅ» መባልን እምቢ ብያለሁ፥ ነፍሴ ትጸየፈዋለች። በመሆኑም ከአምስት ዓመታት በፊት ያወጣሁትን አቋሜን ዛሬም እነሆ እላችኋለሁ። እስከ ሞት ድረስም ያው ነው፥ አይለወጥም።
ኅዳር 1 ቀን 1998 ዓም
አቋሜ፣
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም «ጥንተ አብሶ» የሚባል ነገር ፈጽሞ የሌለባት፣ ከአባታችን ከአዳም በሰው ልጆች ሁሉ ላይ የወረደው የውርስ ኃጢአት እርሷን ግን በጭራሽ ያልነካት ያልደረሰባት፣ ይህም የሆነው የሰው ዘር ሳትሆን ቀርታ ወይም ልዩ ሰማያዊ ፍጡር ሆና ሳይሆን ከአባቷ ከቅዱስ ኤያቄምና ከእናቷ ከቅድስት ሃና የተወለደች ሰማይና ምድርን ለፈጠረ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ እናትነት አስቀድማ የተመረጠችና የታጨች በመሆኗ ለዚህ የመረጣት መንፈስ ቅዱስ ገና በእናቷ ማኅፀን ሳለች በዘር ይተላለፍ ወይም ይቆራኝ ከነበረው የውርስ ኃጢአት ጠብቋታል። እንዳይደርስባትም አንጽቷታል /ንፁህ አድርጓታል/። ምክንያቱም ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። ስለዚህም ከሴቶች ሁሉ የተለየች መሆኗን በቅዱስ ገብርኤል አብሳሪነት በቤተ መቅደስ እያለች ከሦስቱ አካላት አንዱን ወልድን በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደምትፀንስ ተነግሯታል። ተበስሮላታል። በዚያን ሰዓትም የመልአኩን ቃል በመቀበል «እንደ ቃልህ ይደረግልኝ» ስትል ብስራቱን ተቀብላለች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።
እንግዲህ የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርቱ ከጥንት የመጣው የአባቶቻችንም ምስክርነቱ ዛሬ ደግሞ የእኔም እምነት ይሄ ነው። የማስተምረውም የምመሰክረውም ይህንኑ ነው። ይሁንና ዛሬ ዛሬ እንደሚሰማው «እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን መንፈስ ቅዱስ አንጽቷተል ቀድሷታል» የሚለውን አባባል የግድ ከነጻች ኃጢአቱ ነበረባት ማለት ነው አለበለዚያ ከምን አነፃት? በሚል በማይገባ ስህተት ውስጥ ገብተው ይህንኑም በድፍረት የሚናገሩ ሰዎች አልታጡም። ምንም እንኳ መለኮታዊ ጥበብን በሰው ቋንቋ ለመግለጽ አስቸጋሪ ቢሆንም ለማነጻጸርም ቢያዳግትም ለእኛ በሚገባን መንገድ በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት ያህል፦ አንድ ሰው ከመኪና ግጭት አደጋ ለጥቂት ድኗል። ታዲያ ይህን ሰው እግዚአብሔር አዳነው እግዚአብሔር ጠበቀው እንላለን። ሆኖም አድኖታል ጠብቆታል ስላልን የግድ ተገጭቶ ነበር የሚለውን ሃሳብ አያስከትልም። ሳይገጭ እግዚአብሔር ጠብቆታልና። ለመዳን ለመትረፍ መገጨት ወይም ለአደጋው መጋለጥ የግድ የለበትም ፈጦ ከመጣው አደጋ ሊሰወር ይችላልና። ጠበቀው አዳነው ማለት እንችላለን። ነገር ግን አዳነው ስለተባለ ጠበቀው ስለተባለ አለበለዚያ ከምን አዳነው ከምን ጠበቀው ስለደረሰበት ስለተገጨ አይደለም ወይ? ብሎ ማሰብ አለማስተዋል ካልሆነ በቀር ሌላ ሊሆን አይችልም። እንደዚሁም ሁሉ እመቤታችንን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ከአዳም የውርስ ኃጢአት ጠበቃት፣ እንዳይደርስባት አነጻት ስለተባለ ብቻ ያነጸት ስለነበረባት ነው ብሎ ማመን መከራከር ለእኔ ኅሊናዬ የማይቀበለው ነገር ነው። ስለዚህ በትክክለኛው መልክ መሄድ ሲገባ አዲስ ሃሳብና አዲስ ፍልስፍና ማምጣት ትርፉ ውድቀት ነው። ከቶውንስ የፍልስፍና እናቱ መቸገር ነው ተብሎ የለ። ስለዚህ ለሁሉም የሚበጀው በእመቤታችን ላይ ምርምር ማካሄዱ ሳይሆን ይልቁንስ ለአሥራት ሀገሯ ለኢትዮጵያችን ሰላሙን በአማላጅነቷ እንድታወርድልን በረከቷ እንዲበዛልን ፍቅሯ እንዲጨምርልን መማፀን መለማመን እንጂ እግዚአብሔር ያከበራትን ለእናትነት የመረጣትን በማንና በምንም ምሳሌ የማይገኝላትን ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቅድስተ ቅዱሳን በሆነች እናታችን ላይ ቃል መናገሩ አስተያየት መሰንዘሩ በራስ ላይ መልሶ ለመጣል ድንጋይ ማንሳት ነውና ከዚህ መቆጠብ ያስፈልጋል። እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን።

Sunday, December 25, 2011

መርዙ


                          መርዙ


እነሆ ሁለት ባል እና ሚስቶች መኖራቸው ተነገረ፡፡ ግን ፈጽሞ ሊስማሙ አልቻሉም ተባለ፡፡ ቤታቸው የትዳር ቤት ሳይሆን አፍጋኒስታን ይመስል ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም ለምን ሊጋቡ እንደቻሉ ሁለቱንም ያስገርማቸዋል፡፡ አንድ ደራሲ Men from Mars and women from Venus የሚል መጽሐፍ ጽፏል፡፡ እንደተፈጥሯቸው እና ጠባያቸው ቢሆን ኖሮ ወንድ እና ሴት ተጋብተው መኖር የማይችሉ ፍጡራን ነበሩ ነው ጠቅላላ ሃሳቡ፡፡ የትዳር የዘለቄታ ፎርሙላም ይህንን እውነታ ከመረዳት ይመነጫል ባይ ነው፡፡
ታድያ እነዚህኞቹ ከዚህም የባሱ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ እና ጣልያን፣ እንግሊዝ እና አርጀንቲና፣ አሜሪካ እና ቬትናም፣ ይመስላሉ፡፡
 አንዳቸው የሚናገሩት ለሌላቸው አይጥምም፡፡ እንዋደዳለን ብለው ሳይሆን እንበሻሸቃለን ብለው የተጋቡ ይመስላሉ፡፡ ሁለት ተቀዋዋሚ ፓርቲዎች አንድ መንግሥት መሥርተው እርስ በርስ መከራ የሚያዩበት ሀገር ሆኗል ቤታቸው፡፡ «ትዳር ማለት ከውጭ ያሉት እንግባ እንገባ፣ ከውስጥ ያሉት እንውጣ እንውጣ የሚሉበት ነው» የተባለው የተፈጸመው በእነርሱ ነው፡፡
በቤታቸው ቀስ ብሎ የሚናገር የለም፡፡ ባልም ይጮኻል፣ ሚስትም ትጮኻለች፤ እነርሱንም ተከትትሎ ቤቱ ራሱ ይጮኻል፡፡ የሚገርመው ነገር በሩ ሲከፈት ይጮኻል፤ ቴሌቭዥኑ ይጮኻል፤ ጠረጲዛው ሲሳብ ይጮኻል፤ ወንበሩ ሲጎተት ይጮኻል፤ ሁሉም ይጮኻል፡፡
ከአማርኛ ድምፆችች ሁሉ «ዬ» የምትባለው ድምፅ እዚህ ቤት እንዳትደርስ ተከልክላለች፡፡ «እንትናዬ» እየተባለ ሲጠራ ሰማሁ የሚል የለም፡፡ «እ አንተ፣ እ አንቺ፣ ስማ፣ ስሚ» ቤቱ የወታደር ካምፕ ነው የሚመስለው፡፡
እናም ሁለቱም መረራቸው፡፡ መፋታት አሰቡ፤ ግን ፍርድ ቤት ምን እንደሚወስን አይታወቅም፡፡ ለአንዱ አብልጦ ለሌላውም አሳንሶ ቢወስን ሞት መስሎ ተሰማቸው፡፡ ይኼ በቤታቸው ገብቶ የሚያነታርካቸው ሰይጣን ለሁለቱም በአንድ ጊዜ አንድ ክፉ ነገር አመለከታቸው፡፡ አንዱ ሌላኛውን በመርዝ ለመግደል፡፡ አሰቡ ሁለቱም፡፡ እናም ምናልባት መፍትሔ ይሰጠናል ብለው ወደሚያስቡበት አንድ ዐዋቂ ዘንድ ለመሄድ በየግላቸው ወሰኑ፡፡
መጀመርያ ባል ከሚስቱ ተደብቆ ዓርብ ዕለት ወደ ዐዋቂው ቤት ሄደ፡፡ እዚያም ደርሶ ችግሩን ሁሉ ነገረው፡፡ «እኔ ከሚስቴ ጋር መነታረክ ሰለቸኝ፤ አንድ ቀን እንደ ሰው ጥሩ ነገር ሳንነጋገር ይኼው አምስት ዓመት ሆነን፡፡ ነጋ ጠባ ጠብ ነው፡፡ አሁን መረረኝ፡፡ እርሷ ከግራ ጎኔ ሳይሆን ከምላሴ ነው የተፈጠረችው፡፡ የመጣሁት እርሷን ጸጥ አድርጎ የሚገድል መርዝ እንድትሰጠኝ ነው» አለው፡፡ ዐዋቂውም በሃሳቡ ተስማማ፡፡ «ነገር ግን» አለው ዐዋቂው «ሚስትህን በአንድ ቀን በመርዝ ብትገድላት ተጠርጥረህ ትያዛለህ፡፡ ስለዚህ ቀስ በቀስ የሚገድል መርዝ ልስጥህ» አለው፡፡ ባልም ተስማማ፡፡ «ይኼ መርዝ በምግብ፣ በመጠጥ፣ በአልጋ ላይ፣ በወንበር ላይ የሚደረግ ነው፡፡ ሚስትህ ጠርጣራ ናት፡፡ ልትደርስብህ ትችላለች፡፡ ጎረቤቶችህም እንደምትጣሉ ያውቃሉ፡፡ አንድ ነገር ብትሆን ይጠረጥሩሃል፡፡
ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ጠባይህን ቀይር፡፡ እያቆላመጥክ በስሟ ጥራት፡፡ አልጋዋን አንጠፍላት፣ ምግቧን ሥራላት፤ ከውጭ ስትመጣ ስጦታ አምጣላት፤ ሻሂ አፍላላት፤ ራት ጋብዛት፤ ልብሷን ተኩስላት፤ እንዴው በአጠቃላይ ተንከባከባት፡፡ ነገር ግነ ምግብ ስታበላት በምግብ ላይ፣ መጠጥ ስታጠጣት በመጠጡ ላይ፣ ልብሷን ስትተኩስ በልብሷ ላይ፣ አልጋ ስታነጥፍ በአልጋው ራስጌ በኩል ይህንን መድኃኒት ቀስ አድርገህ በትንበት፡፡ ቀስ በቀስ ይገድላታል፡፡ አንተም ትገላገላለህ» አለው፡፡
ባልዬው ተደሰተ፡፡ ያላሰበውን የመፍትሔ ሃሳብ ዐዋቂው በማምጣቱ ዘሎ አቀፈው፡፡ በኪሱ የነበረውን ገንዘብም እንዳለ አወጣ፡፡ ያን ጊዜ ዐዋቂው «አሁን አትከፍልም፤ መድኃኒቱ ሠርቶ ሚስትህ ከሞተች በኋላ ትከፍላለህ፤ አንድ ነገር ግን ጠብቅ፡፡ ሚስትህ  ምናልባት ጠባይዋን ለትቀይር ትችላለች፤ ያን ጊዜ መድኃኒቱ እየሠራ መሆኑን በዚህ ታረጋግጣለህ» አለው፡፡ እየፈነጠዘ መድኃኒቱን ቋጠሮ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡
በማግሥቱ ደግሞ ሚስቱ ተደብቃ መጣች፡፡ «ባሌ ሊገድለኝ ነው፡፡ እኔኮ ባል ሳይሆን ሙቀጫ ነው ያገባሁት፡፡ ሥራው መጨቅጨቅ ብቻ፡፡ አሁን የመጣሁት ከዚህ ሰው ጋር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንድትለየኝ ነው፡፡ መርዝ የለህም ወይ» አለቺው፡፡ «ሞልቷል» አላት ዐዋቂው በፈገግታ፡፡ «የፈለግከውን ያህል ልክፈለህ ስጠኝ» አለቺው፡፡
ወደ ጓዳ ገባና በጨርቅ የተቋጠረ ነገር ይዞላት መጣ፡፡ «እይውልሽ ይሄ መርዝ ነው፤ ግን በአንድ ቀን አይገድልም» አላት፡፡ ተናደደች፡፡ «እኔ ኳ ኮርኳ የሚያደርገውን ነው የምፈልገው» አለቺው፡፡ «እርሱማ አደጋ አለው፡፡ ጤነኛ የነበረ ሰው በድንገት ሲሞት መመርመሩ፣ መጠርጠሩም አይቀር፡፡ ለእኔም ትተርፊኛለሽ» አላት፡፡ አሰብ አደረገቺና «ታድያ ምን ይሻላል?» አለቺው፡፡ «ቀስ በቀስ የሚገድል ይሻልሻል፤ እየታመመ ስለሚሞት ሰው አያውቅብሽም» አላት፡፡ ተስማማች፡፡
«አወሳሰዱ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ በምግብ፣ በመጠጥ፣ በአልጋ፣ በወንበር፣ በልብስ፣ ነው የሚሰጠው፡፡ መጀመርያ ጠባይሺን ቀይሪ፡፡ ያለበለዚያ እሺ ብሎ አይወስድልሺም፡፡ የወደድሺው ምሰዪ፡፡ እቀፊው፣ ሳሚው፣ እጅ የሚያስቆረጥመውን ምግብ ሥሪለት፤ ልብሱን እጠቢለት፤ ፈገግ ብለሽ ተቀበዪው፤ አብራችሁ ተዝናኑ፤ ከጎኑ አትለዪ፡፡ ታድያ ምግብ ስታቀርቢ፣ መጠጥ ስትሰጭው ከዚህ መድኃኒት ትንሽ ብትን አድርጊበት፡፡ ስትተኙም አልጋው ላይ በግርጌው በኩል በተን አድርጊ፡፡ ልብስ ስታጥቢም ይህንን ጨምረሽ አብረሽ እጠቢበት፡፡ በየጊዜው ቤቱን በሚገባ አዘጋጅተሽ በየጥጋ ጥጉ ይህንን በተን በተን አድርጊ፡፡ ከዚያ የፈለግሺው ሁሉ ይሳካል» አላት ዐዋቂው፡፡
በቦርሳዋ የያዘቺውን ሁሉ ገንዘብ ሠፍራ ልትሰጠው ስትል፡፡ «የምትከፍዪው ባልሽ ከሞተ በኋላ ነው» አላት፡፡ ብታደርግ ብትሠራው ሊቀበላት አልቻለም፡፡ መድኃኒቷን ይዛ የሚሆነውን ሁሉ እያሰላሰለች ወጣች፡፡ ልትወጣ ስትል እንዲህ አላት «ባልሽ ጠባዩን መቀየር ይጀምራል፤ ያን ጊዜ መድኃኒቱ እየሠራ መሆኑን በዚህ ታውቂያለሽ»
ቤት እንደገባች ዐዋቂው ባዘዛት መሠረት ቤቷን ታዘጋጅ ጀመር፡፡ ያንን አይታው የማታውቀውን ጓዳ ጎድጓዳ መልክ መልከ ሰጠቺው፡፡ አቧራውን አራገፈች፤ ዕቃውን ቀየረች፤ ወንበር እና ጠረጲዛውን መልክ መልክ ሰጠቺው፤ ግድግዳው ታጠበ፤ አዳዲስ የጌጥ ዕቃዎች በየመልካቸው ተሰቀሉበት፡፡ ከዚያም ወደ ማዕድ ቤት ገብታ እጅ የሚያሰቆረጥም ዶሮ ሠራች፡፡ መጠጡ ተገዛ፤ ቡናው ተፈላ፤ ፈንዲሻው ተፈነደሸ፤ ቤቱ ዓመት በዓል መሰለ፡፡ ሁሉም ነገር ላይ ግን መድኃኒቱ በተን ተደርጓል፡፡
ባል እንደ ለመደው አምሽቶ ከሥራ ገባ፡፡ ዐዋቂው እንዳለው ለሚስቱ ስጦታ የሚሆን ሽቱ፣ ጫማ እና አበባ ይዟል፡፡ መንገድ ላይ ከመድኃኒቱ በተን አደረገበት፡፡ ምን እንደሚፈጠር ባለማወቁ ሲፈራ ሲቸር በሩን መታ፡፡ ድሮ «ምን ትደበድባለህ ከፍተህ አትገባም» የሚለው ድምፅ ነበር የሚሰማው፡፡ አሁን አንድ እጅ ከፈተለት፡፡ ቤቱ ፏ ብሏል፡፡ «ማርዬ ደኅና አመሸሽልኝ» ሲላት ልቧ ወከክ አለ፡፡ «መድኃኒቱ መሥራት ጀመረ ማለት ነው» አለች በልቧ፡፡ እቅፍ አድርጋ ሳመቺው፡፡ ዓይኑንም ጉንጩንም አላመነውም፡፡ ከመጠራጠሩ የተነሣ «እርሷ ናት የሳመቺኝ ወይስ እኔ ነኝ የሳምኳት» እያለ ይጠይቅ ነበር፡፡ ያ ዐዋቂ ያለው እውነቱን ነው ማለት ነው፡፡
ያመጣላትን ሰጦታ ስታይ «በውኔ ነው ወይስ በሕልሜ፣ ወይስ በቴሌቭዥን» አለች፡፡ «የኔ ፍቅር፣ በጣም ነው የምወድህ» አለቺና ወደ ወንበሩ ወሰደቺው፡፡ አብረው ተቀመጡ፡፡ እርሷ ምግብ ልታቀራርብ ወደ ጓዳ ስትገባ በፍጥነት ጎንበስ አለና ወንበሩ ውስጥ መድኃኒቱን በተን አደረገው፡፡
ምግቡን አቅርባ መጠጡን ልታመጣ ሄደች፡፡ አሁንም አወጣና ወጡ ውስጥ በተን አደረገ፡፡
እንደ ጉድ ተበላ፡፡ ተጠጣ፡፡ ከተጋቡ ከሁለት ወር በኋላ ጀምሮ እንዲህ እየተጎራረሱ በፍቅር በልተው አያውቁም፡፡ በሞቴ፣ አፈር ስሆን፣ እየተባባሉ ጨረሱት፡፡ መድኃኒቱ ሠርቷል አሉ በልባቸው፡፡ አምስት ዓመት ሙሉ ያልተጫወቱትን ወሬ ሲያወጉት አመሹ፡፡ አምሽተውም አልቀሩ ወደ እልፍኛቸው ገቡ፡፡ እርሷ ቀድማ ባኞ ቤት ገባች፡፡ እርሱ ተሽቀዳድሞ በራስጌ በኩል መድኃኒቱን በተን አደረገው፡፡ መጣች፡፡ ደግሞ እርሱ በተራው ባኞ ቤት ገባ፡፡ እርሷም በግርጌው በተን አደረገች፡፡ ሁሉም በተኑ፡፡ እነርሱም በፍቅር ብትን አሉ፡፡
ሌሊቱ የፍቅር ሆኖ አለፈ፡፡ ሁሉም በየልባቸው በመድኃኒቱ መሥራት ተደሰቱ፡፡ የሟችን ቀን መቼ እንደሚሆን መገመትም ያዙ፡፡
ያ ሕይወት ቀጠለ፡፡ መገባበዝ ነው፡፡ መዝናናት ነው፡፡ መጨዋት ነው፡፡ መደዋወል ነው፡፡ መነፋፈቅ ነው፡፡ አብሮ መውጣት ነው፡፡ አብሮ መግባት ነው፡፡ ያቺ የጠፋቺው «ዬ» ተመልሳ ገባች፡፡ እርሷም እነ «ዋ»ን ይዛ መጣች፡፡ «ዋ»ም «የኔ ቆንጆ፣ የኔ እመቤት፣ የኔ ጌታ፣ የኔ ማር» የሚባሉ ዘር ማንዘሮቿን ጋበዘቻቸው፡፡ እናም ቤቱ ሞቀ፡፡
አንዳንድ ጊዜ ረስተውት የልብ የልባቸውን ያወሩ ጀመር፡፡ ለምን እንደዚያ ሊሆኑ እንደቻሉ፡፡ መደማማጥ እና መስማማት ለምን እንዳቃታቸው ያወራሉ፡፡ ወዲያው ትዝ ሲላቸው ደግሞ በየግላቸው ተደብቀው መድኃኒቷን በተን ያደርጋሉ፡፡
እየቆዩ ይኼኛው ኑሯቸው እየጣፈጣቸው መጣ፡፡ የማይጠገብ ሆነባቸው፡፡ ተገናኝተው ለመለያየት ሲጨነቁ፤ ተለያይተው ለመገናኘት ሲነፋፈቁ ጊዜ አንድ ነገር አሳሰባቸው፡፡ የቤታቸው ሙቀት ሲጨምር፣ የልባቸው ትርታ ሲንር ጊዜ አንድ ነገር አሳሰባቸው፡፡ አንዱ ለአንዱ ታዛዥ፣ አንዱ ለአንዱ አሳቢ፣ አንዱ ለአንዱ አዛኝ፣ አንዱ ለአንዱ መካሪ ሲሆኑ ጊዜ አንድ ነገር አሳሰባቸው፡፡
ሁለቱም በየልባቸው፡፡ «ይህንን የመሰለ ኑሮ ለምጄ አሁን ቢሞትብኝስ/ ብትሞትብኝስ» ይሉ ጀመር፡፡ ሞት እንዳልናፈቃቸው፣ ሕይወት አጓጓቸው፡፡ ትዳር ምን እዳ ነው እንዳላሉ፣ ፍቺ ምን እዳ ነው ብለው አዜሙ፡፡
እናም ሁለቱም መድኃኒት አድርገዋል፤ ሁለቱም፣ ለመግደል አሢረዋል፡፡ ግን እንዲህ የሚሆን አልመሰላቸውም፡፡ ደግሞ ይህንን ምሥጢር አንዱ የሌላውን አያውቅም፡፡ በዚህ የፍቅር ሞቅታ ውስጥ አንዱ ከሌላው ይህንን ቢሰማ ምን ይላል? እያሉ ተጨነቁ፡፡
ባል ሲከንፍ ወደ ዐዋቂው ቤት ገሠገሠ፡፡
እርሱም እያለቀሰ ተንበረከከ «ሚስቴን መልስልኝ፤ እፈልጋታለሁ መልስልኝ በፊት ከከፈልኩህ ሦስት እጥፍ እከፍልሃለሁ፤ ብቻ መልስልኝ፡፡ እኔ እንደዚህ መሆንዋን መች ዐወቅኩ » እጁን እንደ ሚማጸን ሰው አቅንቶ ለመነው፡፡
«በል» አለ ዐዋቂው፡፡ «ከባድ ነገር ነው የጠየቅከኝ፤ ተነሣና እዚያኛው ክፍል ግባ» አለው፡፡ ተነሥቶ ወደዚያኛው ክፍል ሲገባ ዓይኑን ማመን አልቻለም፡፡ ሚስቱ ተንበርክካለች፡፡ እንዴት መጣች? አለ በልቡ፡፡ ሮጦ ተጠመጠመባት፡፡ «ይቅር በይኝ የኔ ማር» አለ አቅፏት እያለቀሰ፡፡ «አንተ ይቅር በለኝ እንጂ» አለቺው እንዳቀፈቺው፡፡
«ቁጭ በሉ» አለ ዐዋቂው፡፡
ተቀመጡ፡፡
«ሁለታችሁም ባልኳችሁ መሠረት መድኃኒቱን አድርጋችኋል?» ሲላቸው ተያዩ፡፡ ተደናገጡ፡፡ «አንቺም አድርገሻል?» አለ ባል፡፡ «አንተም አድርገሃል?» አለች ሚስት፡፡ «አለቅና» ተባባሉ፡፡
«አላለቃችሁም» አለ ዐዋቂው፡፡ «የሰጠኋችሁ መርዝ አይደለም» ሲላቸው ዘለው ተቃቀፉ፡፡ «እንዲሁ ተራ ቅጠል ነው፡፡ የናንተ ችግር አለመተዋወቅ ነው፡፡ ውስጣችሁ ፍቅር አለ፡፡ ግን ፍቅራችሁን መግለጥ አልቻላችሁም፡፡ ለፍቅር እድል አልሰጣችሁትም፡፡ ትዳር ብዙ በመነጋገር እና በመወያየት ሳይሆን አንዳችሁ ለሌላችሁ በማድረግ ነው የሚገነባው፡፡ አንዱ ሌላው የሚፈልገውን ካደረገ፣ ራሱ የሚፈልገውን እንዳደረገ ይቆጠራል፡፡ ባል ለሚስት፣ ሚስትም ለባል መኖር አለባት፡፡ ባል ራሱን በሚስቱ ውስጥ፣ ሚስትም ራስዋን በባልዋ ውስጥ ማግኘት አለባት፡፡
ብዙ ባል እና ሚስቶች ለመዳር እንጂ ለመጋባት አልታደሉም፡፡ አብረው ይኖራሉ እንጂ አንዳቸው በሌላቸው ውስጥ አይኖሩም፡፡ ትዳር ማለት የሁለት ወንድ እና ሴት ወደ አንድ ጎጆ መግባት አይደለም፡፡ ባል ወደ ሚስት ሚስትም ወደ ባል ውስጥ መግባት እንጂ፡፡ ባል ራሱን ሚስቱ ውስጥ ካገኘው፡፡ ለሚስቱ የሚያደርገውን ለራሱ እንዳደረገው ነው የሚቆጥረው፡፡ ሚስትም እንዲሁ፡፡
ለወደፊቱም ብዙ አታውሩ፣ ግን ብዙ አድርጉ፤ አትዘዙ፣ ታዘዙ፤ እግዚአብሔር ሴትን ሰጥቶሃል፣ ሚስት ማድረግ ያንተ ድርሻ ነው፡፡ ለአንቺም እግዚአብሔር ወንድን ሰጥቶሻል ባል ማድረግም ያንቺ ድርሻ ነው፡፡
እንደ ተቃቀፉ ከዐዋቂው ቤት ወጡ፡፡ እነሆ ለትውስታ እንዲሆን ዛሬም ያንን መድኃኒት ትንሽ ብትን ያደርጋሉ፡፡

                                                          ምንጭ:- ማህበረ ቅዱሳን